የፕራክቲከምና የትምህርት ቤት ትስስር ክፍል
የፕራክቲከምና የት/ቤት ትስስር ክፍል በሀዋሳ መምህራን ትምህርት ኮሌጅ የሚገኝ የአካዳሚክ መርሃ ግብር ቢሮ ነው።. ክፍሉ ሁሉንም የፕራክቲከም ኮርሶችና የኮሌጅና ትምህርት ቤቶች ትስስር ተግባራትን የማስተባበር ኃላፊነት አለበት። ለሁሉም ሰልጣኝ መምህራን የተለያዩ የፕራክቲከም ኮርሶች እንደ የጋራ ሙያዊ ኮርሶች ይሰጣሉ። ፕራክቲከም ለቅድመ አገልግሎት ስልጠና በቅርብ የተጨመረ ኮርስ ነው። የኮርሱ ዋና ዓላማም አዳዲስ ተመራቂዎች በትምህርት ቤት አውድ በመገኘት በንድፈ ሃሳብ የተማሩትን በተግባር እንዲያዳብሩና ተጨባጭ ልምዶችን እንዲያገኙ በማድረግ የማስተማር ክህሎታቸውን ማዳበር ነው፡፡
የፕራክቲከም ዋና ጉዳይ በስልጠና የተገኙ ንድፈ ሃሳቦችን በተግባር ላይ ማዋል ብቻ አይደለም፡፡ ይልቁንም ተግባራዊና ለስራው ሃላፊነት የሚወስድ የመምህር ትምህርት መርሃ ግብርን ማዳበር ነው። የፕራክቲከም ተግባራት፣ ትምህርትንና ተግባርን ያጣመረ ማህበረሰብ ለመገንባትና ከባለ ድርሻ አካላት ለሰልጣኞች ግብረ መልሶች እንዲሰጡ የሚያበረታቱ መድረኮች እንዲሆኑ አዲሱ ፓራዳይም አጽንኦት ይሰጣል፡፡
ስለዚህ የፕራክቲከም ኮርስ ለአንደኛና መለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ለሚሰለጥኑ መምህራን የሚሰጠው፣ ሰልጣኞች ትምህርት ቤቶችንና የመማሪያ ክፍሎችን ሁኔታ እንዲመለከቱ፣ ልምድ ላላቸው መምህራን ረዳት ሆነው እንዲሰሩና ልምድ እንዲያገኙ፣ የተማሪዎችን ባህርይ እንዲያጠኑና በመጨረሻም ራሳቸውን ችለው ማስተማር እንዲችሉ ለማድረግ ነው።
በሁሉም የፕራክቲከም ኮርሶች የተማሪዎች ዋና ዋና ተግባራት የሚሆኑት ተከታታይ ምልከታ ማድረግ፣ ጽብረቃና ለአቻዎቻቸው ግብረ መልስ መስጠት ናቸው፤ እነዚህም ተግባራት ሰልጣኖቹ እርስ በእርስ እንዲማማሩ ከማስቻላቸውም በተጨማሪ ለማስተማር ልምምድ ወደትምህርት ቤቶች በሚሄዱበት ወቅት በኮሌጅ የተማሩትን የይዘት እውቀትና ከትምህርት ቤቶች ያገኙትን ክህሎት አቀናጅተው ወደተግባር እንዲለውጡት ያግዛቸዋል፡፡
የኮሌጅ መምህራን እንዲሁም በአንደኛና መለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ውስጥ ያሉ መምህራን በተለያዩ የፕራክቲከም ተግባራት ማለትም በምልከታ፣ በጽብረቃ፣ በልምምድ ሂደትና በመሳሰሉት ጉዳዮች ላይ አማካሪዎች በመሆን ስራዎችን ያከናውናሉ።
የሀዋሳ መምህራን ትምህርት ኮሌጅ የፕራክቲከምና የት/ቤት ትስስር ክፍል ተጠሪነቱ ለመምህራን ልማት ምክትል ዲን ሲሆን በኮሌጁ መተዳደሪያ ህግ (legislation) ውስጥ የተዘረዘሩ ተግባራትና ኃላፊነቶች አሉት።
ለውጣየሁ ለገሰ ዋቆ (ኤም ኤስ ሲ)
የፕራክ/ት/ቤ/ጉድ/አስተባባሪ
+251916831063